የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ሆነ በስልጣን ዘመናቸው ስደተኞችን የተመለከተው ፖሊሲያቸው ትልቁ ጉዳይ ነበር።
ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ከገቡ በኋላም ፕሬዚዳንታዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው በተለይም የሰባት ሃገራት ዜጎች ቪዛ አግኝተው የአሜሪካን ምድር እንዳይረግጡ እገዳ ማሳለፋቸው ይታወሳል።
ይህንኑ ተከትሎም ትራምፕ ያሳለፉት ዕገዳ፥ በጊዜያዊነትም ሆነ በቋሚነት አሜሪካ መሄድ በሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ላይ ዕገዳና የአመታዊ የቪዛ ኮታ ጥሏል የሚል ወሬ ሲናፈስ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የቪዛ ክፍል ምክትል ቆንሲላ ቼስ ቶምሰን ደግሞ፥ ኢትዮጵያውያን ላይ የተጣለ የቪዛ ኮታ አለመኖሩን ይናገራሉ።
አያይዘውም ባለፈው ዓመት ኤምባሲው ካስተናገዳቸው እና የቪዛ አገልግሎት ከሰጣቸው 18 ሺህ ደንበኞች መካከል አብዛኛዎቹ ተጠቃሚዎች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንም አንስተዋል።
ከዚህ አንጻርም በኢትዮጵያ ላይ የቪዛ ኮታ አለመኖሩን ጠቅሰው፥ ይህ አይነቱ አሰራር ወደፊት ይኖራል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሰባት ሃገራት ስደተኞች ላይ ያሳለፉት ገደብ በፍርድ ቤት እየታየ ሲሆን፥ አተገባበሩ በቀጣይ የሚታይ ይሆናል።
ከዚህ ባለፈ ግን ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሆነው እገዳ ከተጣለባቸው ሰባት ሃገራት የአንዱ ዜግነት ቢኖራቸው ዕገዳው ሊመለከታቸው ይችላል፤ ምክንያቱም ዕገዳው ከዜግነት ይልቅ ግለሰቡ ይዞት በሚመጣው ፓስፖርት ስለሚወሰን።
ቶምሰን አዲሱ የትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ ኢትዮጵያውያን አመልካቾችን የሚመለከት ማሻሻያ እንዳለውም አስረድተዋል።
ይህ ማሻሻያ ከቪዛ ዕድሳት ጋር የተያያዘ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም የቪዛቸው የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ኢትዮጵያውያን በ48 ወራት ውስጥ ቪዛቸውን በዲ ኤች ኤል ልከው ያለ ቃለ መጠይቅ ማሳደስ ይችሉ እንደነበር አስታውሰዋል።
በማሻሻያው መሰረት የጊዜ ገደቡ ወደ 12 ወራት ዝቅ ብሎ ቪዛቸው የተቃጠለባቸው አመልካቾችም 12 ወራት ካለፋቸው ዳግም ቃለ መጠይቅ እንዲያደርጉ ይገደዳሉ ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ተገቢውን ስርዓት ለሚያሟሉ ተጓዦች የቪዛ አገልግሎት የመስጠቱን ሂደት እንደሚቀጥልና፥ ከቀደመው ጊዜ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚኖር ለውጥ እንደማይኖርም ቼስ ቶምሰን ተናግረዋል።
ምክትል ቆንሲላው ኢትዮጵያውያን ቪዛ አመልካቾች አገልግሎቱን በፍጥነት እንዲያገኙ ከፈለጉ ማመልከቻቸውን ፈጥነው ቢያስገቡ የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናሉም ብለዋል።